የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ተቋም ከሙላት ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የእምቦጭ አረም ማስወገጃ ማሽን

Breaking News Social Technology
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ተቋም ከሙላት ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የእምቦጭ አረም ማስወገጃ ማሽን በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተመርቆ ዛሬ ስራ ጀምሯል፡፡

የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት አልሞ እየሰራ እንደሆነ የተጠቆመው የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለይም የእምቦጭ አረምን ለማስወገድ የተለያዩ የፊዚካል እና የስነ ህይዎታዊ ምርምር ስራዎችን እያከናወነ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
እምቦጭን ከጣና ላይ ለማስወገድ በተለይም በአካባቢው ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ያላሳለሰ ጥረት እያደረጉ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ እና ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሚያደርጉትን ጥረት አድንቀዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በእምቦጭ አረም ላይ ያሳዩት መነሳሳት አሁን ለክልላችን በጋራ እና በአንድነት መነሳታችን ያሳያል ነው ያሉት ክቡር አቶ ገዱ፡፡
‹‹ባለምጡቅ አዕምሮ›› ሲሉ በአክብሮት የጠሩትን የሙላት ኢንጂነሪንግ ባለቤትን ለክልሉ ህዝብ ችግር ምላሽ የሚሰጥ ነው እና ላሳለፍከው ጊዜ፣ ላባከንከው ጉልበት እና በስራ ምክንያት የቤተሰብ ፍቅር ለተቀነሰባቸው ቤተሰቦችህ በአማራ ክልል ህዝብ ስም እናመሰግናለን ብለውታል፡፡
‹‹ጣናን በአካባቢው የሚኖሩት አርሶ አደሮች ተጠቅመውበታል፣ ጣናን ከተሞቻችን ተጠቅመውበታል፣ ጣናን የክልሉ መንግስት ተጠቅሞበታል እንዲሁም የፌዴራል መንግስት ተጠቅሞበታል›› ያሉት ክቡር አቶ ገዱ ጣናን ለመታደግ የእያንዳንዳችንን እርብርብ ይጠይቃልም ብለዋል፡፡ በመሆኑም አሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ከእንቦጭ አረም የቆይታ ጊዜ የተማርነው ነገር ቢኖር በአንድ በተወሰነ አካል ብቻ የሚፈታ ችግር አለመሆኑን ነው ብለዋል፡፡
ህዝቡ በጉልበቱ፣ ሙህር በእውቀቱ እና መንግስት በበጀቱ ደግፎ ጣናን መታደግ ይገባል ነው ያሉት፡፡ በተለይም አሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢው ህብረተሰብ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት ብናውቅም አሁን የጀመራችሁት ስራ ግን ህዝብ በአይነ ቁራኛ የሚከታተለው መሆኑን ማወቅና ጠንክሮ እስከመጨረሻ መስራት ይጠበቅባችኋል፡፡ ‹‹አሁን የጀመራችሁትን ስራ በስኬት ብታጠናቅቁ በዚህ ታላቅ ህዝብ ስማችሁ ከፍ ይላል፡፡ ነገር ግን የአንድ ወቅት ስራ አድርጋችሁ ብትተውት ትልቁን ተቋም እና ‹ከአባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳን› ለዘለዓለሙ ታጠለሹታላችሁና በርትታችሁ ስሩ›› ሲሉ ምክረ አዘል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩና ከክልል እና ከፌዴራል መንግስት የመጡ አካላት ማሽኑ የእንቦጭ አረም ሲነቅልም ጎብኝተዋል፡፡
ምንጭ የአማራ ቴሌቪዥይን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *